ሞገደኛው መለስና፤ የሰላማዊ ትግል ተስፋና እውነታ
(ክፍል - 2 መጨረሻ)
የግንቦት
2007 ምርጫ ወያኔ በከፍተኛ አደጋ ላይ ያለ መሆኑን አመልክቷል። የኢትዮጵያን ህዝብ
ለውጥ ፈላጊነት በከፍተኛ ደረጃ ያመለከት ፤ ህዝቡ ለወያኔ ገዢ ቡድን ለጠባብ ዘረኝነት ርዕዮት
ዓለም የጠለቀ ጥላቻ እንዳለው የገለጸ ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ መለስ ዜናዊ እንደገመተው
ያልተከፋፈለ መሆኑን ያረጋገጠ፤ ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ዘመኑ የሚፈቅደው
የፖለቲካ አካሄድ መሆኑን ህዝቡ ጠንቅቆ የተረዳ መሆኑን ወያኔ ራሱ የተረዳበት ፤ የወያኔ ባዶነት
የተገለጸበትና ሞራሉ እስከመጨረሻው የወደቀበት የታሪክ ምእራፍ ነበር። ለዚያም ነው መለስ
ዜናዊ በፍርሀት ስለራደ ቤተ መንግስት መሽጎ በታንክና በመድፍ አዲስ አበባን አስወርሮ፤ ለዚሁ
ዓላማ ባዘጋጀው ልዩ ጦር ሰራዊቱ ህዝብን ያስፈጀው። ኳስ ተከትሎ የሚሮጥ የአስራሁለት ዓመት
ህጻን ፤ የእድሜ ባለጸጋ እናት ጭንቅላታቸውና ደረታቸው ላይ እየተመቱ እንዲገደሉ አዟል ።
ከንግዲህ እየዋሹና ባዶ ተስፋ ለህዝብ እየሰጡ ስልጣን ላይ መቆየት የማይቻልበት ደረጃ ላይ
መደረሱንም በማወቁ ቀጣዩን የስልጣን ዘመን በጦር ሀይል ድጋፍ ለመዝለቅ ተዘጋጀ ።
ከምርጫ
97 በሗላ በጦር ሀይሉም ውስጥ ስልታዊ ያስተዳደርና ያወቃቀር ለውጥ መደረጉን ፤
የረቀቀ የስለላ መረብ መዘርጋቱን ፤ ውስጥ አዋቂ ምንጮች በተለያየ አጋጣሚ ነግረዋል ። ጦር
ሀይሉን መቶ በመቶ በትግራይ ምልምሎች የበላይነት ስር በማስገባት የነበረውን ጥቃቅን ክፍተት
ሁሉ በአየር ሀይል ፤ በምድር ጦር ፤ በፖሊስ ሰራዊት አመራሩን በስልት አጠቃሎ የመቆጣጠር
ስራ መጠናቀቁን ለሰራዊቱ ቅርበት ያላቸው ወገኖች መስክረዋል ።
ኩዴታ ቢታሰብ ለመቆጣጠር የሚቻልበትን ስልት መለስ መንደፉንም ልብ ማለት ያሻል ። የ
አዲስ አበባን ህዝብ የጨፈጨፈው አግአዚ ጦር ከትግረኛ ቋንቋ በቀር የማይናገሩ ከትግራይ አርሶ
አደር ልጆች የተመለመለ ሰራዊት ነው ። ህዝብ በማያውቀው መልኩ በተመሳሳይ ሁኔታ
የተመለመሉ ልዩ ስልጠና ተሰቷቸው በከፍተኛ ቁጥር የተደራጀ ጦር ለህዝብ ግልጽ ባልሆነ መልኩ
በተጠንቀቅ ትግራይ ውስጥ ይገኛል ። የዚህ ጦር ተልኮ በመለስ ላይ ወታደራዊ ግልበጣ ቢሞከር
ፈጥኖ ከትግራይ በመወርወር ኩዴታውን ለማምከን ይዋጋል ።ይህን መለስ በየጊዜው ከሰራዊቱ
የሚያባርራቸው የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ የሰራዊቱ አባላት ይናገራሉ ።
በኢኮኖሚው ረገድ ወያኔዎች ዋናዋናውን ፤ ታማኞቻቸው ትርፍራፊውን በቡድንም ሆነ በነጠላ
በማህበር እየተደራጁ መላውን የሀገሪቱን የስራ መስክ መቆጣጠር በትጋትና በስልት ቀጥሏል ።
ጥንት የነበረው ነጋዴ ሁሉ ከጨዋታ ውጭ እየተደተገ ከሀያ ዓመት ወዲህ የተፈጠሩ አዳዲህ
የህብረተሰብ ክፍሎች ስራውን ተረክበዋል ። አስመጪ ላኪ ፤ አከፋፋይ ፤ አምራች ፤ ቸርቻሪ ፤
ሰሪ ፈጣሪ ሆነዋል ። እነዚህ ሰዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ከሀያ አመት በፊት ትቢያ ላይ ይተኙ
የነበሩ የትግራይ ታጋዮች ናቸው ። ዛሬ ቢሊየነሮች ናቸው ። የት ላይ ይሆን የሚቆሙት
?
የሀገሪቱን ለም የርሻ መሬት ለኢትዮጵያ ህዝብ የወደፊት ህይወት ፤ ለሀገሪቱ የወደፊት ሰላም
አደገኛ በሆነ መልኩ በክፍለዘመን ርቀት መለስ ዜናዊ በስልጣኑ እየሸጠው ነው ። እስካሁን ያመጸ
የተቆጣ ህዝብ የለም ። መለስ ዜናዊ ምክር ቤቱ ውስጥ የሰበሰባቸው ከ
500 በላይ የሚሆኑት
እንስሳት
(የአዲስ አበባውን ምክር ቤት አንዳንድ ሰዎች “መለስ ዙ” ይሉታል ) እንኳ ለምን ይህ
ይሆናል ብለው ፈጣሪያቸው መለስን ለመጠየቅ አልደፈሩም ። የሀገሪቱ የማምረቻ አውታሮች ፤
የንግድ ድርጅቶች ፤ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሑሉ ወያኔና አሽከሮቻቸው በሞኖፖል
ተቆጣጥረውት ሰፊው ህዝብ ከጭሰኝነት ባልተናነሰ መልኩ በቁጥጥራቸው ስር እንዲውልና
ማናቸውንም የፖለቲካ ቡድን በመደገፍ ቢጠረጠር ፤ በቀላሉ ኑሮውን በማፈናቀልና በህይወቱም
በመቅጣት እንዲንበረከክ ይደረጋል ።
ድርቅና ቸነፈር እየተፈራረቀ የሚያረግፈው የኢትዮጵያ አርሶ አደር ቀላሉ የጥቃት ሰለባ ነው ።
የሚያርሳት ኩርማን መሬት የወያኔ ነች ። የሚበትናት ዘርና ማዳበሪያ የወያኔ ነች ። ቡቃያው
በድርቅ ስትጠፋ የልጆቹን ነፍስ የሚያተርፍባት እርዳታ ምንም እንኳ የውጭ መንግስት
ቢያቀርባትም የወያኔ ነች ። ወያኔን ከደገፈ ይሰጠዋል ካልደገፈ እንደራበው ይሞታታል ከነልጆቹ
። የመንግስት ሰራተኛው ካሁን በፊት ባልነበረ መልኩ በወያኔ ተቆጣጣሪነትና አዛዥነት የለትተለት
ተግባሩን ከማከናወን ውጭ አንዳችም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ቢሳተፍ ወይም ቢጠረጠር
ባንዲት ብጣሽ ወረቀት ባንድ የወያኔ ሹመኛ ከስራ ተሰናብቶ ልጆቹን ለማስራብ ይዳረጋል ።ይህ
ነው ባርነት የህይወት ዋስትና ማጣት ። ማን መቸ ተነስቶ ራሱን ነጻ እንደሚያወጣ የሚያውቀው
ጊዜና እግዚአብሄር ብቻ ነው ።
መለስ ዜናዊ በሚመራው የህውሀት ገዢ ቡድን ጭንቅላት ውስጥ ከምርጫ
97 በፊት ከነበረው
ሁኔታ በከፋ መልኩ ለቡድን ስልጣንና ጥቅም ፤ ለአንድ ወገን ፍጹም የበላይነት መሟሟት
የሚለው ውሳኔ ይመላለሳል ። ድሮም ተቀጥቅጦ መገዛትን የለመደ ህዝብ ፤ ሲወጋን የኖረ ህዝብ፤
እኛ ተዋግተን በከፈልነው ዋጋ ተጠቃሚ ሊሆን አይገባም ። የአማራ የበላይነት ተመልሶ
አይመጣም ። የሚለው አስተሳሰብ በመለስ ዜናዊና በሚመራው ቡድን ጭንቅላት ውስጥ
ይመላለሳል ።
የዘረኛው ቡድን ፋሽሽታዊ አገዛዝ የገባው ወጣት ፤ መለስ ባመከነው ሰላማዊ አብዮት የነበረውን
ንቁ ተሳትፎ ለማዳፈን ያኔ ቢጨፈጭፈውምና ሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ እንደማይሰራ በቂ
ተሞክሮ ቢኖረውም ፤ በ
1966 ተሲያት ላይ እንደነበሩት ቀደምቶቹ ፋኖ ብሎ የለውጥ ሀዋርያ
ለመሆን ቆርጦ ለመነሳት የዘገየ ይመስላል ። በገዢው ቡድን ውስጥ ከፍተኛ እብሪትና የልብ ልብ
እንዲኖር ያደረገ ክስተት ነው ። መለስ ዜናዊ መልእክቱ ግልጽ ነው ። በግድ እንጂ በውድ
ስልጣን አይለቅም ። የወጣቱን ቅስም ለመስበር አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት ያምናል ።
በአጠቃላይ በህዝቡ ላይ እያደረሰ ያለው የአካልም ሆነ የስነልቦና ጥቃት እንዳለ ሆኖ ፤ ወጣቱን
ከመከፋፈል ባሻገር ፤ አላጎበድድም ፤ በጥቅማጥቅም አልገዛም የሚለውን ወገን ፤ የዚያ ድርጅት
የዚህ ድርጅት ደጋፊ እያለ ከትምህርት ፤ ከስራ ማፈናቀሉን ፤ ማሰሩን ፤ ማንገላታቱን ቀጥሏል ።
ምክንያት እየፈጠረ ወጣቱን በግፍ መግደልና ማሰር ትውልዱ በፍርሀት እንዲርድና ከትግል ራሱን
እንዲያገል ለማድረግ እንደሚያስችለው መለስ ያምናል ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የ
አካዳሚክ ነጻነታቸውን በተመለከተ ላቀረቡት ጥያቄ በሞት እንዲቀጡ ያደረገው ጥያቄው ለስልጣኑ
አስግቶት ሳይሆን ወጣቱ በስርዓቱ ላይ ቢነሳ ሊገጥመው የሚችለውን ምላሽ እንዲያውቀው
ለማድረግ ነው ። በስልሳዎቹ መጨረሻና በሰባዎቹ መጀመሪያ ላይ ደርግ ያደረሰው ከባድ
ጭፍጨፋ ወጣቱ ትግል ለምኔ ብሎ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የሀገርን ጉዳይ እንዲተወው ምክንያት
ሆኖ ነበር ። ወያኔ ከዚያ የደርግ እርምጃ የተማረው ነገር እንዳለ ልንጠራጠር አይገባም
።አንዳንዶች በደርግ ዘመን ያለቀውን ወጣት አሁን ኢህአደግ ከፈጀው ጋር በማነጻጸር ወያኔ ብዙ
አልገደለም ሊሉ ይችላሉ ። ደርግ እራሱን የቻለ ጦርነት ተከፍቶበት ነበር ያን ሁሉ ትውልድ
የፈጀው ። ወያኔ ምንም የሚያሰጋው ነገር በሌለበት እራሱ ጠብ እየጫረ ነው በመግደል ላይ ያለው
። ሀይል የተሞላበት እንቀስቃሴ ቢጀመር ፤ በጠንካራ አንድነት ፤ በመላ አገሪቱ እጅግ በተቀናጀና
በተደራጀ መልኩ ባንድ ጊዜ ፤ በአንድነት ፤ካልሆነ በስተቀር ባጭር ጊዜ መለስ ዜናዊ ከሩዋንዳ
ባለተናነሰ መጠን በሰላማዊ ዜጎች ላይ እልቂት ይፈጽማል ። የሆነው ሆኖ አሁንም የኢትዮጵያ
ህዝብ ዛሬ ነገ ሳይል በአንድነት ለነጻነቱ ካልተጋደለ መለስ ዜናዊ እስከመጨረሻው እየገደለ
መኖሩን ይቀጥላል ። ለኢትዮጵያ ህዝብ አሁን የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው ። አንዴ ፤
ባንድነት ፤ በቁጣ ተነስቶ እንዳንበሳ ሰውነቱን ማርገፍገፍ ፤ የወረሩት ዝንቦችና ትንኞች ከትከሻው
ላይ ይረግፋሉ ። ይጠፋሉ ። ትልቁ ቁምነገርና ተስፋ ወያኔን በሚፈልገው መንገድ ሊታገለው
የተዘጋጀ ትውልድ መነሳቱ ላይ ነው ። ሀያ ዓመታት አለፉ ። ሀገር በምጥ ከረመች ። ጀግና ግን
እስካሁን አልተወለደ ይሆን
?
አብዛኛው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርስቲ ተማሪ እንደቀድሞው ትውልድ ብሄራዊ ስሜቱ
ኢትዮጵያዊ አንድነቱ በውስጡ እያንሰራራ እንዳለ ሁሉ ፤ ወደ ዘርና ክልል አስተሳሰብ ዘቅጠው
ለህውሀትም ሆነ ለሌሎች ዘረኛ ቡድኖች መሳሪያ እየሆኑ ያሉ ወጣቶች መፈጠራቸው አልቀረም ።
እነዚህ ሰዎች የሚመስላቸውን መፍጠራቸው መሳካቱንም ያመለክታል ። በዘር ተቧድነው
በድንጋይና በጩቤ የሚዋጉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ማየት የቻልንበት ዘመን ላይ ደርሰናል ።
ትውልድ ሲዘቅጥ እንዲህ ነው ።
እርግጥ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ክፍለ ህዝባቸውን ወይም በቀጥታ አባባል ብሄረሰባቸውን በተመለከት
መገፋት እንዳይኖር ፤ የመብት ረገጣ እንዳይኖር ፤ እንባ ጠባቂ ሆኖ መገኘት ፤ የሰብዓዊ
መብትና የእኩልነት መነፈግ እንዳይኖር ፤ ለመከላከል ያስችላል ። ያም ቢሆን አንዱ ለሁሉም
ሁሉም ለአንዱ መጮህ የበለጠ ሀይልና ትርጉም አለው ። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሄሮች ሁሉ
ቋንቋቸውና ባህላቸውን እንዲያበለጽጉ እንዲያሳድጉ መርዳት ፤ መብታቸው እኩልነታቸው
እንዲረጋገጥ መታገል ፤ ሀላፊነቱ የዚያ ብሄር አባላት ብቻ ሊሆን አይገባውም ። መላው የሀገሪቱ
ህዝብ እንጂ ። ሕጻናት አፍ በፈቱበት ቋንቋ እስከ አንደኛ ደረጃ ማማር አለባቸው ። ቋንቋቸው
ማሰቢያቸው ነውና ። እያንዳንዱ ብሄር የጋራ መግባቢያ የሚሆነውን አንድ ወይም ሁለት ብሄራዊ
ቋንቋ እንደ ዜጋ የመማር የማወቅ ግዴታም ይኖርበታል ። አንዲት የጋራ ሀገር አለችንና
።ኢትዮጵያ በምድሯ ላይ የበቀሉ ሁሉ በእኩልነት የሚበለጽጉባትና የሚያበለጽጓት ሀገር
እንድትሆን መታገል አርአያነት ያለው ተግባር ነው ። ነገር ግን ያዘር ይህንን ዘር ረግጦታል ።
ይህን ከዚያ ፤ ያን ከዚህ ነጻ አወጣለሁ ፤ የሚለውን ወያኔያዊ የዘቀጠ አስተሳሰብ ይዞ መንገታገት
ለማንም ወገን የማይበጅ ስህተት ላይ መውደቅ ነው ። ምናልባትም የዚህ ዝቃጭ አስተሳሰብ
ልክፍተኞች ከኢትዮጵያ ለመጨረሻ የሚጠፉበት ዘመን አሁን ይሆናል ። የመጨረሻዎቹ እነመለስ
ዜናዊ ሊሆኑ ይችላሉ ። በከፋፋዮች አስተሳሰብ ፤ በዘረኝነት ፍልስፍና ዙሪያ ተጠላልፈው
የሚዳክሩ ወጣቶች ፤ አይናቸውን ገለጥ አድርገው ፤ ተወልደው ስላደጉባት ሀገርና በፍቅር
ስለሚመለከታቸው ህዝብ ቆም ብለው ቢያስቡ ፤ ከዘረኝነት አስተሳሰብ ወጣ ብለው ስለ አብሮነትና
ስለ ወንድማማችነት ቢያስቡ ፤ ዘርን ከዘር ነጻ ስለማውጣት ሳይሆን ተጭኖን የሚኖረውን ግዙፉን
ድህነት በጋራ ተዋግተን ከርሀብ ከበሽታ ከእርዛት ራሳችንን ነጻ ብናወጣ ለልጆቻችን የህይወትን
ነጻነት ብልጽግናን እናወርሳለን ። ዛሬ በዘረኝነት አስተሳሰብ ውስጥ የዘቀጡ ወጣቶች መልካም
ቢያስቡ የተሻለች ሀገር የሚፈጥር የተሻለ ትውልድ ሊሆኑ ይችላሉ ። የዘረኞች የጥፋት መሳሪያ
ከመሆን ይድናሉ ። እርግጥ ጭፍን የዘር ጥላቻ ከቤተሰብም ከአካባቢም ሊወረስ ይችላል ።
መሰረት ሊኖረውም ላይኖረውም ይችላል ። የትምህርት ትልቁ ጥቅሙና ትርጉሙ ግን የባህሪ
ለውጥ ማምጣት ማስቻሉ ነው ። ጥሩና መጥፎን መለየት የሚያስችል የሚያመዛዝን አእምሮ
መገንባት ማስቻሉ ነው ።
በዘር የመከፋፈል በሽታ ከመገዳደልና ከመጠፋፋት በቀር ለትውልድ የሚያመጣው ሰናይ እሴት
የለም ። በዋናነት የፍልስፍናው ባለቤት የሆነውን የወያኔና የባህሪ ወንድሞቹን እድሜ ከማራዘምና
በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መከራ ከመጫን በቀር የሚያመጣው አንዳችም ፋይዳ የለም ።
ዘረኝነት ለሱማሊያ በጀ
? ለሩዋንዳ በጀ ? ለዩጎዝላቢያ በጀ? ለሂትለር በጀ ? እኛም
ከተጠመቅንበት ለማናችንም አይበጅም ።
በማንኛውም የዓለም ህዝብ ዘንድ እንዳለ ሁሉ በሀገራችንም ውስጥ በየህሄረሰቡ መካከል ያለው
የቋንቋ የባህል ያመለካከት ልዩነት ፤ ብሄራዊ እሴት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ፤ አንዳንድ በህብረተሰቡ
ውስጥ ያሉ በአሉታዊ መልኩ የምንወስዳቸው ተራ ችግሮች ፤ ባካባቢ ፤ በቋንቋ ፤ በባህል ፤
በአኗኗር ፤ በልምድ ፤ የመናናቅ ተራ አመለካከቶች ፤ ህብረተሰብን በማስተማርና ህግ በማውጣት
ሊታረሙ የሚችሉ ናቸው እንጂ ሕዝብን ለመከፋፈል የሚያራግቡአቸው ፤ የፖለቲካ ልዩነት
መፍጠሪያ መሳሪያ ሊሆኑ የሚገባቸው ችግሮች አይደሉም ። ያንድ ትልቅ ሀገር ሰፊ ህዝብ ይቅርና
ያንድ እናት ያንድ አባት ልጆች እንደየመልካችንና እንደየባህሪያችን ፤ ቅጽል ስም እንሰጣጣለን ።
እንበሻሸቃለን ።
ለምሳሌ ሁለት ዘላን ብሄረሰቦች በግጦሽ አካባቢና በከብት መሰራረቅ ከጥንት ጀምሮ የሚጣሉ ካሉ
፤ ዛሬ ወያኔ ያንን ቅራኔ የፖለቲካ ቅርጽ እየሰጠው እንዲዋጉ እንዲጣሉ በዘር እየከፈለ
ችግራቸውን እያከፋው ይገኛል ። ሰላማቸውን እንዲያደፈርሱና በየአካባቢያቸው መረጋጋት
እንዳይኖር ባጠቃላይ ህብረተሰቡ ውስጥ ሽብር እንዲነግስ ለማድረግ ይጠቀምበታል ። ይህም
መለስ ዜናዊ ብልሀት አድርጎ የያዘው ከቅኝ ገዢዎች አሰራር ያጠናው የአስተዳደር ስልት ነው ።
ለተማረውም ሆነ ላልተማረው የኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ ነው ። የኢትዮጵያን ህዝብ በነቂስ መድረስ
ቢቻል አንዱ ባንዱ ላይ በቀላሉ ተቀስቅሶ እየተጠፋፋ ለወያኔ የግፍ አገዛዝ መንገዱን ቀና
ከሚያደርገው ፤ የሚሰብኩትን እንዳልሰማ እያለፈ በወያኔ አንጻር ሁሉም ዜጋ አንድ ሆኖ የአገዛዙን
እስንትንፋስ ለማሳጠር መነሳት አለበት ።
ዛሬ በየዓለሙ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በህዝባችን ላይ ሰቆቃና ግፍ በተፈጸመ ቁጥር የምናደርገው
ስናጣ የዓለም ሕብረተሰብ እያልን በያገራቱ መንግስታት ኢምባሲዎች ደጃፍ እየቆምን ሮሮ
እናሰማለን ። ህዝባችንን ታደጉልን እያልን እናለቅሳለን ። በደርግም ስርዓት ሁኔታው ይኸው ነበር
። ለምሆኑ የአለም ህብረተሰብ ማነው
? እስከዛሬ ለጮህነው ጩኸት ማንስ ምላሽ ሰቶ በኢትዮጵያ
የግፍ አገዛዝ ይቁም ብሎ የእውነት ድጋፉን ሲሰጠን ታየ
? የኛ የዋህነት ከየት ይጀምራል ?
ለጥቅማቸውና ለሰላማቸው ስጋት ያልሆነባቸውን እንዲያውም ታማኝና አገልጋያቸውን መንግስት
እናስወግደው እርዱን ስንላቸው ፤ የሚያውቁትና የሚጠቀሙበት መንግስት ተወግዶ መጪው ለነሱ
ምን ይዞላቸው እንደሚመጣ አውቀውት ነው ከታማኛቸው ጋር የሚቀያየሙት
? ያለውን መንግስት
አስወግደው ሌላ ማስቀመጥ የሚያተርፋቸው ከሆነ ፤ የተነሳበትን መርዳት ብቻም አይደለም
እራሳቸው ጦር ይዘው እንደሳዳም ፤ እንደጋዳፊ ይዘምቱበታል ። የሚገዛውን ህዝብ ቢያርድም
ቢጨፈጭፍም ስልጣን ላይ ያለው ወገን ከሆነ ለነርሱ አትራፊው የቆመውን ፈረስ መጋለብ ነው ።
ዛሬ የዓለም ፈላጭ ቆራጭ የሆኑት በየአገሩ እየዘመቱ አላጎበድድም ፤ አላገለግልም ያላቸውን
መንግስትና ሀገር ሁሉ የሚያፈርሱት አሜሪካኖች የአለም ህብረተሰብ ፤ የአለም መንግስትም
የሚባሉት እነሱው ሆነዋል ። ከሶቬት ህብረት መውደቅ በሗላ ለራሳቸው የእስላም ጠላት ፈጥረው
ሽብር ውስጥ የወደቁ ናቸው ። የኛን አሸባሪ ሊዋጉልን ቀርቶ አሸባሪያችሁን እወጋላችሗለሁ
ያላቸውን አቅፈው ደግፈው የሚጉዋዙ ናቸው ። በምስራቅ አፍሪካ ዋናው የጉዳያቸው አስፈጻሚና
ተላላኪያቸው መለስ ዜናዊ መሆኑን መዘንጋት የለብንም ። መለስ ዜናዊ የነሱ ድጋፍ እንዳይለየው
ብቻ ነው የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማይመለከት ጉዳይ ልጆቻችንን
(ጦር ሰራዊቱን) በየቦታው
እያዘመተላቸው የልጆቻችን ህይወት በከንቱ እየጠፋ አሜሪካኖቹ የሰራዊታቸውን ህይወትና
ለጦርነት የሚያወጡትን ወጭ ያድናሉ ። የሚያሳዝነው ነገር ይህ በየቦታው እየተላከ በከንቱ
የሚሞተው ሰራዊት አዝማቹ ወገን የሚከፍለውን አበል እንኳ ወያኔ እየተቀበል ወደ ካዝናው
ሲሰበስበው የሰራዊቱ ልጆችና ቤተሰብ በኑሮ ውድነትና በረሀብ ሲሰቃዩ ለምን አፈሙዙን በወያኔ
መሪዎች ላይ አዙሮ እራሱንና የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻ ለመውጣት መነሳት እንዳቃተው ነው ።
እኛው ከኛው ጋር አንድነታችንን አጠናክረን የሀገር ውስጥ አርበኞቻችንን መደገፍና የተቻለውን
ሁሉ ማድረግ እንጂ የአለም ህብረተሰብ እያልን አሜሪካ ወይም እንግሊዝ መቶ ነጻ እንዲያወጣን
የሩቁን መጠበቅ ጅልነት ወይም ፈሪነት ነው ። እንነሳ
! እንነሳ! ወያኔ እያሰለሰ ነጣጥሎ እየመታን
ሁላችንንም ሳይጨርሰን ፡ ሁላችንም ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠርን ዘሮች አንድ ላይ ተነስተን
ራሳችንን እናድን
!!!!!
አንድ ከሆን እናሸንፋለን ፤ ከተለያየን እንወድቃለን
!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !
No comments:
Post a Comment