የሀየሎም አርአያ ግድያ ምስጢር
የሀየሎም አርአያ ግድያ በጥንቃቄ እና አደናጋሪ በሚመስል ስልት እንዲቀላጠፍ መለስ እና ኢስይያስ አፈወርቂ በጥብቅ ምስጢር ከወሰኑ በኋላ ከሻ’ኣቢያ እና ህወሀት ደህንነት የተመረጡ ነብሰ ገዳዮች ተልእኮ ይቀበላሉ። በሻ’ኣቢያ በኩል ዑመር ገረወይናይ (በንግድ ስራ ስም አዲስ አበባ ነዋሪ ሆኖ እስከ ኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ድረስ የቆየ) ፤ ወዲ ዑመር (የዑመር ገረወይናይ ልጅ እና የሻ’ኣቢያ ደህንነት አባል - ሀየሎም ላይ የተጠነሰሰውን የግድያ ሴራ ለማጠናቀቅ አዲስ አበባ ቆይቶ አስመራ የተመለሰ) ፤ እንዲሁም ጀሚል ያሲን - ሀየሎም ላይ ጥይት በመተኮስ ሴራው ተፈፃሚ እንዲሆን ያደረገው ነብሰ ገዳይ።
ሀየሎም አርአያ
የባድመ ጀግኖች
በህወሀት በኩል ሴራው ውስጥ በቀጥታ የተሳተፉ፦ መለስ ዜናዊ ፣ ክንፈ ገብረመድህን ፣ አሁን የደህንነት ሹም የሆነው ጌታቸው አሰፋ ፣ ብርሀነ (የጌታቸው አሰፋ አማች ሲሆን ወዲ ዑመር አዲስ አበባ በቆየበት ግዜ በሹፌርነት አገልግሎት የሰጠ) ፣ አሰፋ ጉሬዛ (ጀማል ያሲን ተኩሶ ሀየሎምን ከገደለ በኋላ ተይዞ ብቻውን ተቆልፎበት በነበረበት ግዜ የምርመራ ቃሉን የተቀበለ እና በየግዜው ጀሚልን ያነጋግር የነበረ ብቸኛ የህወሀት ደህንነት አባል ፤ ልዑል የሁዋላ (የህወሀት ደህንነት አባል እና ናይሮቢ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመድቦ በርካታ የውስጥ ምንጠራ ግድያዎችን በማስፈፀም እንደተሳተፈ የሚነገርለት)።
ወደ ዝርዝሩ እንውሰዳችሁ -
1ኛ - ጀሚል ያሲን ማን ነው? - ይህ ኤርትራዊ ግለሰብ ‘እንጀራ ፍለጋ ስደት ወጣሁ’ በሚል ሽፋን ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ዘለግ ላሉ ዓመታት የኖረ ሲሆን እውነቱ ግን ውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን በህቡዕ ለማጥመድ የተመደበ የሻ’ኣቢያ ሰላይ ነበር። ህወሀት ስልጣን በተቆጣጠረ ማግስት የጀሚል መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን ተወስኖ በፍጥነት እንዲዛወር ተደርጓል።
መለስ ዜናዊ ‘የኤርትራ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው’ ብሎ በአደባባይ የሚሟገት ብቻ ሳይሆን ይህነኑ አቋም የሚያረጋግጥ መድብል የፃፈ ‘ወዳጅ’ እንደሆነ ሻ’ኣቢያ እና አባላቱ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለሆነም አዲስ አበባ መለስ እጅ መውደቋ ‘ነፃ’ ለመውጣት የነበረውን ጥያቄ በማያሻማ መንገድ ከማረጋገጡም በላይ የሻ’ኣቢያ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በመረጡት ቦታ ፣ ባሻቸው መታወቂያ መኖር እና ተግባራቸውን ማቀላጠፍ እንደሚችሉ ዋስትና አግኝተዋል። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ጀሚል መቀመጫውን ከሰውዲ አረቢያ ወደ አዲስ አበባ ማዛወር መርጧል። (ከባድመ ጦርነት ወዲህ ተመልሰው ለመጡ ኤርትራውያን ‘ስደተኞች’ ምቾት ሲባል ዛሬም የሚወጣውን ደንብ እና መመርያ ልብ ይሏል)።
ጀሚል ያሲን አዲስ አበባ እንደተዛወረ እራሱን የንግድ ባለሀብት አድርጎ በማስተዋወቅ 300,000 (ሶስት መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር) ከብሔራዊ ባንክ ‘ብድር’ እንዲወስድ ይፈቀድለታል። ከህወሀት የውስጥ ሹማምንት ጋር ለመገናኘት የተመቻቸለትን ልዩ ‘ፈቃድ’ በመጠቀም ’ኢሕአዴግ’ በሚጠራቸው ይፋዊ ስብሰባዎች ላይ እየተገኘ የህወሀት ተቆርቋሪ ወዳጅ መሆኑን አስመስክሯል።
2ኛ - ዑመር ገረወይናይ እና የሻ’ኣቢያ ደህንነት ሰራተኛ የሆነው ወዲ ዑመር (አባትና ልጅ) –
ዑመር ገረወይናይ አዲስ አበባ ለረጅም አመታት የኖረ ‘ነጋዴ’ ሲሆን በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መፈንዳት ማግስት እንደ ሌሎች ኤርትራውያን ከአገር የተባረረ ግለሰብ ነው። ዑመር በወቅቱ የደህነነት ሚኒስቴር ምክትል ከነበረው ጌታቸው አሰፋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንደነበረው ይታወቃል። የዑመር ልጅ ወዲ ዑመር የሻ’ኣቢያ ደህንነት ሰራተኛ ሲሆን የሀየሎምን ግድያ አፈፃፀም ለመምራት አዲስ አበባ ሲመጣ አባቱ ባቀረበለት ተሽከርካሪ የጌታቸው አማች በሆነው ወጣት ብርሀኔ ሾፌርነት ተግባሩን ከሂልተን ሆቴል ሲያቀላጥፍ ቆይቷል። ወጣት ብርሀኔ በሾፌርነት እንዲያግዝ የተመረጠበት ምክንያት መዲናችንን ጠንቅቆ ስለሚያውቃት በትራፊክ በኩል ችግር እንደሌለበት ስለሚታወቅ፤ እንዲሁም በዕድሜው ወጣት እንደመሆኑ ጠለቅ ብሎ ስለ ፖለቲካ ሴራ ጥርጣሬ ውስጥ አይገባም በሚል ግምት ነበር።
ወዲ ዑመር አዲስ አበባ ገብቶ ማረፊያውን በሂልተን ሆቴል ባደረገ ማግስት ስለ ተልዕኮው መሳካት እንዲያማክራቸው የተሰጠውን ዝርዝር በመከተል ተግባሩን ጀምሯል። በየዕለቱ ሰዎች ያገኛል ፣ አንዳንድ ቀን ከማንም ጋር ሳይገናኝ በከተማይቱ ተዘዋውሮ ሲመሽ ሆቴል ይመለሳል። ይሁንና በየምሽቱ ከአስመራ ጋር በልዩ የራዲዮ መገናኛ አማካኝነት የደረሰበትን ደረጃ ሪፖርት ያቀርባል። ከብዙ ሰዎች ግንኙነት ማድረጉ ቢታወቅም ከጀሚል ያሲን 2
(የሀየሎም ገዳይ) ጋር ፊት ለፊት የተገናኙት ግን በመጣ በአስራ አምስተኛው ቀን ማብቂያ ገደማ ነበር - የተገናኙት ሁለት ግዜ ብቻ እንደነበረም ተረጋግጧል።
ወዲ ዑመር በጥር ወር መጀመሪያ ሳምንት ላይ ተመልሶ ወደ አስመራ በጠዋት ከመብረሩ በፊት በሼፌርነት አገልግሎት ለሰጠው የጌታቸው አሰፋ አማች ብርሐኔ ‘የመጣሁበት ጉዳይ እንዲሳካ ላደረክልኝ ድጋፍ ከልብ አመሰግናለሁ’ በማለት እርካታውን ገልፁዋል።
እናም ወዲ ኡመር አዲስ አበባን ለቆ በወጣ ዕለት አመሻሽ ላይ ሀየሎም አርአያ በመኖሪያ ቤቱ ዘና ብሎ የሰራ አካሉን እያዝናና ነበር። ይሁንና የቤቱ ስልክ ተደወሎ ሲያነሳ መስመር ላይ ወዳጁ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ ቀርቦ ምሽቱን አብረው እንዲዝናኑ ይጋብዘዋል። ሀየሎም ያን ዕለት ለመውጣት ስሜት እንደሌለው በመግለፅ ይቅርታ ጭምር ቢጠይቅም ፕሮፌሰሩ የልመና ያህል ‘ለኔ ስትል’ ተቸገር በሚል ይማፀነዋል። በጨወታ ወዳድነቱ እና ከተራው ዜጋ ጋር በቀላሉ ተቀላቅሎ የመላመድ ባህሪ እንዳለው የሚነገርለት ሀየሎም የወዳጁን ተማፅኖ መጋፋት ሀፍረት ሆኖበት በመጠጥ ቤት ለመገናኘት ይወስናሉ። ብዙ ግዜ እንደሚያደርገው ሁሉ ሀየሎም ጠባቂ ወይም አጃቢ ይዞ መዝናኛ ስፍራ አልሄደም።
እንድርያስ እና ሀየሎም ተገናኝተው መጠጥ አዘው ብዙ ሳይቆዩ ጀሚል ሀሰን ወደ መጠጥ ቤቱ ዘልቆ በመግባት ሰላምታ ተለዋውጦ ከነሀየሎም ጠረጴዛ ይቀላቀላል። ከአፍታ በሁዋላ ሰላማዊ ጨዋታ ይመስል የነበረው የቃላት ልውውጥ ከረር ወዳለ ንትርክ ይለወጣል። ሀየሎም ባጋጠመው በዚህ አጉል ንትርክ አፍሮ ይሁን ወይም የሚጠረጥረው ጉዳይ ይኑር ባይታወቅም ዝምታን መርጧል - በስንት የጦር ፍልሚያ ላይ በወኔ የተዋደቀ ጀግና ከፊቱ ተቀምጦ ከሚያንጓጥጠው ግለሰብ ጋር አፍ ለመካፈት አለመሻቱን መረጠ።
የሀየሎምን ትዕግስት ያጤነው ጀሚል መላልሶ ሲናገር እንደተሰማው "ምን ትኮፈሳለህ?... የኛ ተጋዳላይ .. ድንቄም ዝነኛ ኮማንደር… አንተን ብሎ ጀግና … ተናገር እንጂ - መኩራትህ ይሆን እንዴ?..." እያለ ዘለፋውን ቀጠለ። የመጣበትን ተልዕኮ ጠንቅቆ የሚያውቀው ጀሚል የሀየሎምን ንዴት ለመጫር ሲል ለገላጋይ የማይመች ሆኖ ገፍቶ መጣ። ሀየሎም ቢቸግረው መጨረሻ ላይ "ጥፋልኝ ከፊቴ አንተ ሰው!" ሲል ጀሚልን ገፈተረው።
በዚህ ወቅት ጀሚል ያሲን ከቡና ቤት ተጣድፎ ወደ መኪናው በመሄድ ሽጉጥ ይዞ ይመለሳል - ወደ መጠጥ ቤቱ ከተመለሰ በሁዋላ አንዳች ቃል ሳይተነፍስ ሀየሎም ላይ ደግኖ በመተኮስ ወለሉ ላይ ይጥለዋል። በረጅሙ የትግል ውጊያ ዘመን የተለያየ የመቁሰል አደጋ ደርሶበት መልሶ እያንሰራራ እንደ ነብር ይዋጋ የነበረው ጀግና ፤ ጥይት አይበሴ እየተባለ ስንኝ የተቋጨለት ዜማ የተቃኘለት ትግል አርበኛ ዛሬ ግን አካሉን እንኳ ማላወስ ተስኖት እስከ ወዲያኛው ተሰናበተ።
ከትግራይ ጎጆዎች እንደ ንብ ተመው ፣ ለመልካም ዘመን መባት እና ለሰብአዊ መብት መረጋገጥ ሲሉ የተዋደቁ ሽህዎችን ያዋጋ እና ያኮራ ስመ ጥር ሀየሎም አርአያ ከመጠጥ ቤት ወለል ላይ ለዘላለሙ አሸለበ።
በጦር ሜዳ ሙያ የተካኑ የደርግ አዋጊዎች ተኩሰው ያልጣሉት ጠናካራ ታጋይ በሚያምናቸው እና የትግል አጋሮቼ ናቸው ብሎ እምነቱን በጣለባቸው ረጃጅም ሙጃዎች ሴራ ወጥመድ ስር ወድቆ ከመሸታ ቤት ወለል ላይ ተዘረጋ። አሟሟቱን አቀናብረው ቀምመው - እንደ ጀግና ሳይሆን እንደ መሸተኛ እንዲሞት ፈረዱበት።
የሀየሎም ገላ መቀዝዙን ያረጋገጠው ነብሰ ገዳይ ጀሚል ያሲን በመጣበት ተመልሶ በመውጣት ጨለማው ውስጥ ተሰወረ። እውነትነቱ በማያሻማ መንገድ በጥናት ክፍላችን ባይረጋገጥም ሀየሎምን ለመግደል ጀሚል በዚያን ዕለት የተጠቀመበትን ሽጉጥ ያገኘው በወቅቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮማንደር ከነበረው የህወሀት ታጋይ አራንሺ ገብረመስቀል እንደነበር የሚጠቁሙ ፍንጮች መኖራቸውን ግን ሳናነሳ አናልፍም።
ነብሰ ገዳዩን ሰዶ ማሳደድ
ተራሮችን ‘አንቀጥቅጧል’ ተብሎ የተሸነገለው መላው የህወሀት ታጋይ በሀየሎም ዜና ዕረፍት በሽብር ተናወጠ። በተለይም ስለ አሟሟቱ የተሰራጨው ወሬ የሠራዊቱን አከርካሪ ዘልቆ በሚሰረስር ምሬት ድንጋጤን ፈጠረ - ብዙ ታጋዮች የፍፃሜው ደወል ያስተጋባ መሰላቸው።
የተፈጠረውን ድንጋጤ እና መሸበር ለማርገብ ሲባል ‘ነብሰ ገዳይ ኤርትራ ተወልዶ አደገ እንጂ ትውልዱ ትግራይ’ ነው የሚለውን ወሬ በአንድ አቅጣጫ በማናፈስ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በክንፈ ገብረመድህን እና ጌታቸው አሰፋ ትዕዛዝ በርካታ ኤርትራውያን እየተከበቡ እስር ቤት ተወረወሩ። አህያው እና ዳውላው ለነ ክንፈና ጌታቸው ምስጢር ባይሆኑም ዱላቸውን ግን ዳውላው ላይ አዘነቡት። ከዱላው ለግዜው ያመለጠው ጀሚል ተልዕኮውን አጠናቆ ሲያበቃ አስቀድሞ በተሰጠው መመርያ መሰረት ኤርትራ ኤምባሲ ገብቶ መሸገ - ‘ተሸሸገ’።
ገዳዩን ለመያዝ አሰሳ የወጣው የነክንፈ ቡድን በሞቀ ክትትል ላይ መሆኑን ታፍሰው እስር ቤት እየታጎሩ ያሉትን ኤርትራውያን አሀዝ በማጣቀስ እያመለከተ ነው። በማግስቱ ደግሞ ቀደም ሲል ከኤርትራ የመጣውን የግድያ አቀነባባሪ (ወዲ ዑመር) በሹፌርነት አንዲያገለግል ተመድቦ የነበረው የጌታቸው አሰፋ አማች ብርሐኔ በኢትዮጵያ አየር መንግድ ተጭኖ ወደ ጀርመን ለዕረፍት እንዲሄድ ሽኝት ተደረገለት። ብርሐኔ ዕረፍት አድርግ በሚል ጀርመን እንዲሄድ አማቹ የአውሮፕላን ቲኬት ስጦታ ሲያበረክትለት ጉዳዩ ድንገተኛ ቢሆንበትም ሳያመነታ ተቀብሎ ወደ ኮሎኝ ተጓዘ - እንደዚህ ያለ ‘ሰርፕራይዝ’ የት ይገኛል!!
ሀየሎም በተገደለ ሁለተኛ ቀን ከህወሀት ደህንነት ጆሮ የገባ ‘ሰበር-መረጃ’ እንዳመለከተው ነብሰ ገዳዩ ጀሚል ያሲን በኤርትራ ኤምበሲ ‘ተሸሽጎ’ ይገኛል የሚል ነበር። ሁዋላ እንደታየው - ስለ እስረኛው አያያዝ ከኤርትራ ሹማምንት ጋር በጋራ ምክክር ከተደረገ በሁዋላ ጀሚል ያሲን ለኢትዮጵያ 3
ፖሊስ ተላልፎ ተሰጠ። ጀሚል ከኤርትራ ኤምበሲ ተይዞ ሲወሰድ በአንደበቱ ሲናገር እንደተሰማው ‘ህዝባዊ ግምባር (ሻ’ኣቢያ መሆኑ ነው) የሰጠኝን ግዳጅ ተወጥቻለሁ… እኔ የህዝባዊ ግምባር አባል እንጂ ወንጀለኛ አይደለሁም’ በማለት ለኢትዮጵያ ፖሊስ መተላለፉ ቀደም ሲል ከነበረው የግድያ እቅድ ጋር እንደሚፃረር አመልክቷል።
በምን የተነሳ ጀሚል ያንን ቃል እንደተናገረ የምንገነዘበው ግን ከዚህ ቀጥሎ በምናነበው ሂደት ነው፦
ጀሚል ያሲን በቁጥጥር ስር ከዋለበት ቀን አንስቶ ለሚቀጥሉት ሁለት ተኩል ዓመታት ማለትም እስከተረሸነበት ቀን ድረስ ከማንም እስረኛ ወይንም ጠያቂ ጋር ሳይገናኝ በጥብቅ ጥበቃ ስር እንዲቆይ ተደርጓል። የተረሸነው ኤርትራ በትግራይ በኩል ወታደራዊ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ ነበር።
ጀሚል ‘ፍረድ ቤት ቀርቦ ሞት ስለተፈረደበት ተረሽኗል’ የሚል ሀተታ በራዲዮ ቲቪ እንዲነገር ቢደረግም ይህ ግን ጉዳዩ በሕጋዊ የፍርድ ሂደት እንደተጠናቀቀ ለምዕራብ አገሮች ፍጆታ ተብሎ የቀረበ እንጂ አንዳችም ግልፅነት ያለው የፍርድ ሂደት አለመካሄዱን ሁሉም ያውቃል። በብቸኛ ክፍል የእስር ቆይታው ወቅት ከአሰፋ ጉሬዛ በስተቀር ጀሚል ያሲንን አነጋግሮ የሚያውቅ ማንም ሰው የለም።
አሰፋ ጉሬዛ - ከባዶ ስድስት እስከ ናይሮቢ ሀርሊንግሀም
አሰፋ ጉሬዛ በህወሀት ድርጅት ውስጥ ለረጅም ዘመን በደህንነት ሥራ የቆየ እና በተለይም ባዶ ስድስት እየተባለ በሚታወቀው እና (አሁን ኦሀዮ ኮለምበስ ነዋሪ የሆነው ብስራት አማረ ያዝበት የነበረ) ከህወሀት አፈነገጡ የተባሉ አባላትን እና እስረኞችን በማሰቃየት እና በመግደል ዝነኛ በሆነው የበረሀ እስር ቤት አባል የነበረ ነው። ይህ የህወሀት ታማኝ ገራፊ በጭካኔው የተመሰከረለት በመሆኑ የሀየሎምን ግድያ በሚመለከት ከጀማል ያሲን ቃል እንዲቀበል እና ምርመራ እንዲያካሂድ ሙሉ ስልጣን ተሰጠው።
ጀሚል ያሲን ከአሰፋ ጉሬዛ በስተቀር የሰው ዘር ሳያይ… ምናልባትም ‘በስምምነት መሠረት’ ከነገ ዛሬ ነፃ እለቀቃለሁ ብሎ ተስፋ እንዳደረገ ከነምስጢሩ እንዲወገድ ተደርጓል - ጀሚል ምንም ይበል ምን ዝርዝሩን ለቋሚም ሆነ ለታሪክ - ለዘመድም ይሁን ለጠላት እንዲያቆይ ግዳጅ የወደቀው መርማሪው አሰፋ ጉሬዛ ላይ ብቻ ነበር።
ይሁንና ጀሚል ያሲን ስለፈፀመው ግድያ የሰጠው ቃል ፣ የዘረዘረው ምስጢር አሰፋ ጉሬዛ እጅ እንደሚገኝ በተለይ የነመለስ ቡድን ጠንቅቆ ያውቃል። ይህ ምስጢር በሆነ ሰበብ አፈትልኮ ከሠራዊቱ ዘንድ ቢደርስ መዘዙ እጅግ አደገኛ እንደሆነ የማይገነዘብ የለም - ስለዚህ መፍትሄ ይሻል።
አሰፋ ጉሬዛ ከጀሚል ያሲን የተቀበለውን ታላቁን የግድያ ሴራ በህሊናው እንደተሸከመ በዲፖሎማትነት ሹመት አግኝቶ ወደ ናይሮቢ ኢትዮጵያ ኤምባሲ እ.ኤ.አ. መጋቢት 1998 ተላከ። ናይሮቢ ሲደርስ ማረፊያ አፓርተማ ተዘጋጅቶለታል - ስፍራው ሀርሊንገሀም የሚባል ከዝነኛው ያያ ሴንተር ዝቅ ብሎ የሚገኝ ሰፊ ግቢ ነበር። ቤት ብቻ ሳይሆን መኪናም ተዘጋጅቶለታል - ሲቪል ታርጋ ያላት እና በኤምባሲው ከ1983 ዓም ጀምሮ የደህንነት ተጠሪ ሆኖ በቆየው ልዑል የሁዋላ ስትነዳ የቆየች ነጭ ቶዮታ ካምሪ። አቀባበል ያደረገለትም ይኸው ልዑል የተባለው ነባር የህወሀት ፀጥታ ሠራተኛ ነበር።
ልዑል የሁዋላ ማነው?
ልዑል በትግራይ የአክሱም አካባቢ ተወላጅ ሲሆን በ1970ዎቹ ዓመታት ህወሀት ጋር ክፍሊ ህዝቢ በተሰኘው ውስጥ መቀላቀሉ ይነገራል። በበረሀ ብዙም ሳይቆይ በአንድ አጋጣሚ አሰሳ በወጡ በደርግ ድጋፍ በተደራጁ የትግራይ ወጣት አብዮተኞች እጅ ማህበረ-ደጓይ በተሰኘ መንደር ውስጥ ይያዛል። እጁን አሳልፈው ለመንግስት የሰጡ ቢሆንም በእስር ብዙም ሳይቆይ ይፈታል። ሁዋላ በ1974 ዓም አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ገብቶ እስከ 1976 ድረስ በኢኮኖሚክስ ዘርፍ ትምህርቱን ይከታተላል። ይሁንና በ1976 ማገባደጃ ላይ በህቡዕ ለህወሀት እንደሚሰራ ተደርሶበት በደርግ ደህነነት ከዩንቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ተይዞ ማዕከላዊ ይታሰራል። ልዑል አሁንም በእስር ብዙ ሳይቆይ 1979 - 80 አካባቢ ከማዕከላዊ በዋስ ይፈታል። ከዚህ በሁዋላ እንስቃሴው በደህነነት እይታ ውስጥ መሆኑን ተገንዝቦ ይመስላል በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ በመሰደድ መርሳቤት በተሰኘው (ከናይሮቢ 400 ኪሎሜትር ሰሜን ምስራቅ) የስደተኞች ሰፈር ይጠለላል። ህወሀት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ልዑል በጉስቁልና ይኖርበት ከነበረው የመርሳቤት ስደተኛ ሰፈር ታጅቦ በቀጥታ ናይሮቢ ይመጣና አዲስ እየተደራጀ ባለው በናይሮቢ የህወሀት (ኢትዮጵያ) ኤምበሲ ደህንነት ሹም ወንበር ይሰጠዋል።
ልዑል የሁዋላ በናይሮቢ ቆይታው አንዳንድ ኢትዮጵያውያንን በተለይ የፖለቲካ ተሳትፎ የነበራቸውና ወያኔ ያሰጉኛል ያላቸው ሰዎች እንዳጠፋ ይነገርለታል። ለአብነት ያህል የቦረናው ተወላጅ እና በደርግ ዘመን የቦረና ክልል አስተዳዳሪ የነበሩት ሻለቃ ጃተኒ (መባፅዮን) አሊ ይገኙበታል።
የግዳጅ ፍፃሜ በናይሮቢ
አሰፋ ጉሬዛ የዲፖሎማት ካባ ተጎናፅፎ ናይሮቢ ሲገባ አቀባበል ያደረገለት ልዑል የሁዋላ ነበር - በግል ታርጋ የሚያሽከረክራትን ንብረትነቷ የኤምባሲ የሆነችውን ቶዮታ መኪናም እንዲጠቀምበት ሰጥቶታል። አጠገቡ ተቀምጦ ከተማውን እያለማመደ ሰነባብቷል። አንድ ምሽት ግን አሰፋ ቤቱ ሊገባ ከቅጥር ግቢው ደርሶ ዘበኛው በር ይከፍታል ብሎ ሲጠብቅ ሌሎች እንግዶች ጎትተው አውጥተው በጥይት ጠቅጥቀው ይገድሉታል። ናይሮቢ የመኪና ዘረፋ የተለመደ ወንጀል በመሆኑ ዜናው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሲደርስ ብዙ ሰው አዘነ። ተደጋግሞ እንደሚደርሰው እና መኪናቸውን የተዘረፉ ግለሰቦች በናይሮቢ ቲቪ ዜና ማሰራጫ ላይ ቀርበው ሲናገሩ እንደሚሰማው የጦር መሳሪያ ደግነው መኪና የሚነጥቁ ዘራፊዎች ሰው የሚገድሉት አሻፈረኝ ብሎ ለመቋቋም የሚከጅል ሰው ሲያጋጥማቸው ነው። ታዲያ አዲሱ ዲፕሎማት እንግዳ በመሆኑ ከመኪና ውረድ ሲሉት ስላንገራገረ ገደሉት ተብሎ በሰፊው ተወራ - ክፉ ዕድል ገጠመው ብሎ ሰሚው አዘነ - ቆይቶም ጉዳዩን ረሳው። በወቅቱም ሮይተርስ የተባለው የዜና ድርጅት ግድያውን እንዲህ ሲል ዘገበ። 4
NAIROBI (APR 3) - A senior Ethiopian diplomat was killed April 3 [1998] in the Kenyan capital.
First Secretary Assefa Gebreselassie [aka Assefa Gureza] was shot dead and his car stolen after robbers approached at the gates of his home in Nairobi's Hurlinghan suburb at 10:30 pm local time.
እዚህ ላይ አንባቢ ልብ እንዲለው የሚያሰፈልግ ነገር ቢኖር - አሰፋ ጉሬዛ ሲያሸከረክራት አምሽቶ በዘራፊዎች ተወሰደች የተባለችው ነጭ ቶዮታ ካምሪ ከስድስት ወራት በሁዋላ ወደ ኤምባሲው ቅጥር ግቢ ተመልሳ በደህነነት ወንበር ላይ አዲስ ለተመደበው የማነ ለተባለ ወጣት ዲፕሎማት ትሰጣለች። በወቅቱ የኤምባሲው ሰዎች ሲናገሩ እንደተሰማው ‘በኬንያ ፖሊስ ዕርዳታ እና ክትትል መኪናችን ተገኘች’ ተባሏል - አሁንም ጉዳዩን የጠረጠረ ማንም የለም (በንቅዘት ዝናን ያተረፈው የኬንያ ፖሊስ አንድ መኪና ስድስት ወር ሙሉ ሲያሳድድ ነበር አገሪቱን ለሚያውቅ የሚዋጥ ነገር አልነበረም)።
ገሀድ የሚታወቅ ሀቅ ቢኖር ግን ናይሮቢ መኪና የሚዘረፈው በቡድን በተደራጀ ማፊያ መሆኑን ፣ የተዘረፉ መኪኖች ውለው ሳያድሩ ወደ ጎረቤት ታንዛንያ እና ዩጋንዳ እንደሚሻገሩ ፣ በቁም ወይም ብትንትናቸው ወጥቶ ለመለዋወጫ እንደሚሸጡ ነው። ናይሮቢ የኖረ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህን ሀቅ ይመሰክራል። የተዘረፈ መኪና መልሶ ይገኛል ማለት ከቶ ዘበት ነው። ለአሰፋ ጉሬዛ ሞት መነሻ የሆነችው ካምሪ ግን ተአምር ሰርታ መልሳ መንገድ ላይ ወጣች።
በመጨረሻም
አሰፋ ጉሬዛ የሀየሎም አርአያን አገዳደል ሂደት እና የሴራውን ዝርዝር በሚገባ አግኘቷል። አሰፋ ብዙዎች እንደሚገልፁት ምስጢር መቋጠር የማይሆንለት በተለይ ሞቅ ሲለው የገረፈውንም ያስለፈለፈውንም ፣ የገደለውንም ሁሉ በሰም እየጠራ እንደሚዘከዝክ ይነገራል። ይህን ባህሪውን እያወቁ ያንን የምርመራ ግዳጅ ለምን ሰጡት ብሎ መጠየቅ ቢቻልም ግለሰቡ በምርመራ ስራ ብዙ ዘመናት መቆየቱ ፤ ጉዳዩ አስጊ እየሆነ ሲመጣ ግን ሰውየውን ከማስወገድ ሌላ አማራጭ አልነበራቸው።
አሰፋ ጉሬዛ ከተገደለ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ የተፈራው ደረሰ - ሻእቢያ ኢትዮጵያን ወረረ። "ከሻእቢያ ጋር ያለን ግንኙነት በወርቅ የተገነባ፣ በደም ቀለም የተፃፈ ታሪክ ነው፤ ሻእብያ ኢትዮጵያን ይወራል የሚሉ የጠላ ቤት አሉባልተኞች ናቸው!" እያለ የህዝቡን የጦርነት ስጋት ሲያጣጥል የኖረው መለስ ዜናዊ ደግሞ የሚይዘው፣ የሚጨብጠው ጠፋ። ህዝቡ እና የውጭ ሚድያዎች ሳይቀሩ "መለስ ዜናዊ የቁም እስረኛ ሆኗል" ብለው ቢያወሩምና ለፍርድ የሚያበቁ ከባድ ወንጀሎች ቢኖሩትም፣ ፀረ-ሻእቢያ ተብለው የተወራላቸው ከፊሎቹ የህወሓት አመራር ግን የህዝቡን ድጋፍ ሳይጠቀሙበት እንዳንቀላፉ ቀሩ። መለስም ያቺን ቀውጢ ሰዓት ለማለፍ ሲል የራሱ እርምጃዎች ይወስድ ጀመር፤ አንዱም ጀሚል ያሲንን የሚስጥር ፋዩሉን እንደታቀፈ ወደ መቃብሩ መከተት ነበር።
የመለስ ታማኝ ካድሬዎች ሀየሎም አርአያ በእጀ መናኛ መሸታ ቤት ተገደለ ብለው በሰፊው ያሰራጩት ወሬ የፈፀሙትን ወንጀል ሊደብቀው አልቻለም። አማቹን ጀርመን አገር በመላክ አንዱን የአይን ምስክር ብርሐኔን ባህር ማዶ ያቆየው የወቅቱ የህወሀት ደህንነት ሚኒስትር ጌታቸው አሰፋ ጉዳዩ ተርስቷል በሚል እምነት ሳያድርበት አልቀረም። ብርሐኔ ሚስት አግብቶ ልጅ ወልዶ ለስድስት አመት ይኖር ከነበረበት ኮሎኝ ተመልሶ አዲስ አበባ የተንደላቀቀ ህይወት እየኖረ ይገኛል። ለሁሉም ግዜ አለው… እውነት ግን አንድ ቀን በኢትዮጵያ የፍርድ አደባባይ እልባት ታገኛለች።
ሀየሎምስ አለፈ … ተከታዩ ማን ይሆን?
ኢትዮሚድያ - Ethiomedia.com
October 24, 2011
No comments:
Post a Comment