Tuesday, November 15, 2011
1
የሃየሎም አርአያ ግድያ ምስጢር
ክፍል 1 በኢትዮሚዲያ ጥናት ክፍል የቀረበ - ጥቅምት 2004
አዲስ አበባ ላይ የተፈፀመው የሃየሎም አርአያ ግድያ ጉዳይ ከአስራ አምስት ዓመታት በሁዋላ ዛሬ ድረስ ብዙዎችን እንዳጠያየቀ ነው። ከግድያው ጀርባ የተደበቀ ሴራ እንዳለ አብዛኛው የውስጥም ሆነ የውጭ ታዛቢ ቢጠረጥርም እንቆቅልሹን ለመፍታት ግን ቀላል ሆኖ አልተገኘም። ግድያው ተራ አምባጓሮ ያስከተለው መዘዝ ነው በሚል በመንግስት መገናኛ አውታሮች ተደጋግሞ መሰራጨቱ ደግሞ እውነቱን አበጥሮ ለማውጣት ርቆ ለመሄድ ሊኖር የሚችለውን ፍላጎት አዳክሞታል። ይሁንና የጥናት እና መረጃ ክፍላችን በተለያዩ አቅጣጫዎች በጥንቃቄ በሰበሰባቸው ማስረጃዎች አስደግፎ ሀቁን ለሁሉም ለማቅረብ መብቃቱን በዚህ ዘገባ ያረጋግጣል። ሀየሎም ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ሴራ ‘እንዲወገድ’ መደረጉን እና ጥይት ተኩሶ ህይወት በማጥፋት በነብስ ገዳይነት የተወነጀለው ኤርትራዊው ጀሚል ያሲን ደግሞ የሴራው ምዕራፍ አንዲቋጭ ግዳጅ የተሰጠው ተራ መልዕክተኛ መሆኑን እንደሚከተለው እናቀርባለን።
አንባቢን በቅድሚያ ማስገንዘብ የምንወደው ነገር ቢኖር በሃየሎም ግድያ ዙርያ እጃቸው የተነከረ ሴረኞች እውነቱ እንዴት ገሀድ ሆነ? በሚል ድንጋጤ ወይም ንዴት ሊያድርባቸው እንደሚችል እና "ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት ስለተገደለ የወያኔ ጦር መሪ ማን ግድ አለው?" ለማለት እንደማይመለሱ እናውቃለን… ፤ ግድያው ተቀብሮ እንዲቀር የሚፈልጉበት በርካታ ምክንያት መኖሩን ጭምር ይህ ጥናታዊ ዘገባ ይጠቁማል።
በሃየሎም ግድያ ዙርያ የተደበቀው ምስጢር ይፋ መውጣቱ የመለስ ዜናዊ አውሬአዊ ተፈጥሮ የት ድረስ ርቆ እንደሚሄድ ይበልጥ ለመረዳት ያስችለናል። ጥናታዊ ዘገባው የመለስን አቋም የማይቀበሉ ዜጎች እንዴት በተቀነባበረ ሴራ እንደሚወገዱ በተጨባጭ ያሳያል ፤ ብሎም የስልጣን ኮርቻውን አደላድሎ ለመቆየት ሲል የሚፈፅመውን ግፍ ሳያሰልሱ ማጋለጥ ለሚደረገው ፍትሀዊ የሕዝብ ትግል ጠቃሚ መሆኑን ያመለክታል።
በመለስ ዜናዊ አመራር ስር የሚፈፀም ፖለተኪዊ ግድያ አፈፃፀሙ በሙሉ እንደ ትያትር አስቀድሞ በየደረጃው የሚነደፍ በመሆኑ ለተራው ብዙሀን ዜጋ ቀርቶ በቀለም ለገፋው ጭምር በቀላሉ የሚነበብ አይደለም። ሴራ መኖሩን ብትጠረጥር እንኳ ‘መለስ ከደሙ ንፁህ ነው’ የሚል ግምት እንዲያሳድር ይደረጋል።
ሃየሎም አርአያ ቡና ቤት በተነሳ አምባጓሮ በጀሚል ያሲን ተገደለ፤ ክንፈ ገብረ መድህን በሌላ የወያኔ ሻለቃ እጅ ተገደለ፤ ቀድሞ የወያኔ ኪነት አባል የነበረው ታዋቂው ኢያሱ በርሀ ወይንም የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረው እና በመለስ ዜናዊ ከተባረሩት ባለስልጣኖች አንዱ የነበረው ገብረመስቀል ሀይሉ በደም ብዛት ድንገት ሞቱ… ተክሌ ሀዋዝ ግዳጅ ላይ ሞተ … ስንቱ ተቆጥሮ ይዘለቃል? የመለስ እጅ በነዚህ እና በሌሎች ሽህ ዜጎች ደም ጨቅይቷል።
ወደ ተነሳንበት አቢይ ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ‘ሚስቱ ተኩሳ ገደለችው’ ስለተባለው ኮሎኔል በርሔ ሸቢያ ጥቂት እናስታውስ - ኮለኔል በርሔ ቆፍጣና የውጊያ መሪ መሆኑ የተመሰከረለት፣ በኤርትራ የወረራ ውግያ ወቅት በዛላአምበሳ-ፆረና ግምባር አኩሪ መቋቋም ያደረገ ኮማንደር ነበር። ተደጋግሞ እንደተሰማው "መለስ ዜናዊ ከስልጣን ካልተወገደ ኤርትራን ማሸነፍ ያዳግተናል" እያለ ሰራዊቱን ያስጠነቅቅ እንደነበር ይታወቃል። መረጃው ከመለስ ጆሮ መድረሱ እንደማይቀር ግን ሳይገነዘብ ቀርቷል። በወቅቱ ውጊያው አስጊ ደረጃ ላይ እንዳለ ቢታወቅም ኮለኔሉ አዲስ አበባ ለወታደራዊ ምክክር እንዲመጣ ትዕዛዝ ይደርሰዋል። ታዲያ አዲስ አበባ በደረሰ ምሽት ኮሎኔል በርሔ በመኖሪያ ቤቱ ሞቶ መገኘቱን የሚዘግብ ዜና በኢትዮጵያ ቴሌቭዢን ይሰራጫል። ዜናው አክሎ እንዳቀረበው ‘ኮሎኔል በርሔ ሚስቱ በተኮሰችበት ጥይት የሞተ ሲሆን ሚስቱም ወዲያውኑ ራሷን መግደሏ ታውቋል’ ይላል። የመለስ ግፍ በዚህ አላበቃም የቴሌቭዢን ዘጋቢ ከስፍራው ተገኝቶ ሽጉጥ የጨበጠች ሴት በደም ባህር ውስጥ ተዘርግታ እንዲታይ ተደርጓል። በማግስቱ - ባልና ሚስት ባንድ ቀን ለቅሶ አፈር እንዲለብሱ ሆነ - በቀብር ላይ የተገኘው ቤተዘመድ እና ውስጥ አዋቂ ግን ጮሆ ቢያለቅስም በሽኩሹክታ ‘ይሄ ባንዳ ሁለቱንም ባንድ ቀን በላቸው’ ይል እንደነበር ታዛቢዎች ይገልፃሉ። ከዚህ ዘግናኝ ግድያ ጀርባ ያለው ሀቅ እንደሚያረጋግጠው ኮሎኔል በርሔ የተገደለው በውደቅት ምሽት ‘እንኳን ደህና መጣህ’ ሊሉት ቤቱ በመጡ የደህንነት ‘እንግዶች’ ሲሆን የሁለት ልጆቹ እናት የሆነችው ሚስቱም በድንጋጤ ግራ ተጋብታ ለማምለጥ ስትሞክር ተገድላለች። ከዚያም እሬሳዋን ሽጉጥ አስታቅፈው ‘ባሏን ገድላ እራሷን አጠፋች’ የሚል ዜና አሰረጩ…።
በሀየሎም አርአያ ግድያ ዙርያ ያሉ ጭብጦች
የግድያው ሴራ እንዲቀላጠፍ ግዳጅ የተሰጠው ለኤርትራዊው ጀማል ያሲን እንደነበር ሁሉም የሚያውቀው ነው። ጭብጥ ለማሳት ሲባል ጀማል ያሲንን አንድ ተራ ‘ጥጋበኛ ወይንም ሰካራም ኤርትራዊ’ አድርጎ ለመቀባት የመለስ ዜናዊ ታማኝ ካድሬዎች ያላደረጉት ሙከራ የለም።
በ’ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ’ ታሪክ ውስጥ ከተፈፀሙት የግድያው ሴራዎች ሁሉ በውስብስበነቱ ወደር የማይገኝለት በሃየሎም አርአያ ላይ የተፈፀመው ነው ብንል ማጋነን አይሆንም። በተራው ተዋጊ ዘንድ ገናና ስም የገነባው ሃየሎም በጦር ሜዳ አመራር ብቃት የላቀ ተሰጥኦ እንደነበረው በሰፊው ተነግሯል - ከደርግ ጋር በተደረገው ግብግብ እፁብ የተሰኙ የጦር ሜዳ ድሎችን አስመዝግቧል። ይሁንና ይህ ታላቅ የጦር መሪ ከመለስ ዜናዊ ጋር እጅግ የተቃቃረ ግንኙነት እንደነበረው ብዙዎች ያውቃሉ። በተለይም ደግሞ ኤርትራን በሚመለከት መለስ የሚያራምደው ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅምን የሚጎዳ መሆኑን በማመልከት ሃየሎም ተቃውሞውን በይፋ ደጋግሞ የገለፀ መሆኑ ምስጢር አልነበረም።
መለስ ዜናዊ አሁን የጦር አዛዥ አድርጎ ከሾመው ሳሞራ ዩኑስ ጋር በየዕለቱ በመገናኘት የቅርብ ግንኙነት ሲገነባ ከሃየሎም ጋር ግን አንዲት ቀን እንኳ ቡና አብረው ጠጥተው እንደማያውቁ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚሹ የውስጥ አዋቂዎች ይነገራሉ። እንደነዚህ ምንጮች ከሆነ "በተራው አባል ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅ የሆነው ሃየሎም በህይወት መቆየቱ ለመለስ ስልጣን እጅግ አስጊ መሆኑ ታምኖበታል - መፍትሔው እንዲወገድ ማድረግ ብቻ ነበር… የሆነውም ይኸው ነበር"። 2
በ1987 ጥቅምት ወር ላይ ሳሞራ ዩኑስ ከፍተኛ የጦር አዛዦችን በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ስበሰባ ጠርቶ ኤርትራ በቀይ ባህር ላይ ያሉት የሀኒሽ ደሴቶች ይገባኛል ብላ ከየመን ጋር ጦርነት ውስጥ ስለመግባቷ በማውሳት የኢትዮጵያ ጦር ከኤርትራ ጎን ተሰልፎ የመንን መውጋት አንዳለበት ይገልፃል።
የስበሰባው ተሳታፊ የነበረው ሃየሎም የኤርትራን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል በየመስኩ መለስ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በማስታወስ የቀረበውን ሀሳብ ፈጥኖ በመቃወም ግልፅ በሆነ ቋንቋ "አንድም ኢትዮጵያዊ ወታደር የሌላ አገር ጦርነት መዋጋት የለበትም" የሚል ቃል ይናገራል - ይህን ግልፅ እና ድፍረት የተመላበት ተቃውሞ የሰማው ተሰብሳቢ ፀጥ ረጭ አለ። የሃየሎም አቋም በወታደሩ ዘንድ ተደማጭነት እንደሚኖረው እና የመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ውድቅ ሊሆን እንደሚችል የተረዳው ስብሰባውን በመምራት ላይ የነበረው ሳሞራ ዩኑስ የቡና እረፍት እንዲሆን ያሳስባል። ከአስራ አምስት ደቂቃ የቡና እረፍት ሲመለሱ የሰብሳቢነቱን ወንበር ከሳሞራ በመውሰድ መለስ ዜናዊ እራሱ ጉዳዩን መልሶ አንዲያዩት በሚል ቀጠለ።
በስብሰባው መክፈቻም "ቀደም ሲል ሃየሎም የሰነዘረውን ተቃውሞ አዳምጫለሁ…" በማለት ኤርትራ እንደ ማንኛውም የጎረቤት አገር የምትታይ ባለመሆኗ - ብሎም የጋራ መከላከል ስምምነት የተፈራረምን በመሆኑ ‘ልዩ ወዳጃችንን የመደገፍ ግዴታ አለብን’ በሚል ሃየሎም ተቃውሞውን እንዲስብ ይጠይቃል።
ሃየሎም በበኩሉ ኢትዮጵያ አንዲት የደም ጠብታ ለኤርትራ ሲባል መገበር እንደሌለባት በአፅንኦት በመግለፅ "የሻ’ኣቢያ ደም በገነፈለ ቁጥር…" ከተነኮሳቸው የጎረቤት አገሮች ጋር ጦርነት መግጠም አይገባንም አለ። ስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ከነበሩት ከፍተኛ የቶር አዛዦች መካከል ግን አንዳቸውም ሃየሎም የሚለውን ለመደገፍ እና ቃል ለማሰማት ድፍረት አላገኙም። (ለማስታወስ ያህል) እንደ ስዬ አብርሀ የነበሩ ‘ተጋፊዎች’ ቀደም ሲል ከጦሩ አካባቢ ርቀው ትግራይ የኤፈርት ስራ አስኪያጅ ሆነው ‘በግዞት’ እንዲቀመጡ ተደርጓል።
የሃየሎም አቋም የማይለሳለስ መሆኑን የተረዳው መለስ መፍትሔው ‘ደንቃራውን ማስወገድ’ ብቻ እንደሆነ ለራሱ አረጋግጧል። የመጀመሪያው እርምጃ - ለኤርትራ ድጋፍ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ጦር ዝግጅት ሃየሎም በማይሳተፍበት ኮሚቴ እንዲቀናጅ በምስጢር ተወስኖ ጉዳዩን መለስ እና ሳሞራ ብቻ እንዲመሩ ተደረገ።
(አሁንም ለማስታወስ ያህል - መለስ ዜናዊ ባንድ በኩል ከኤርትራ ጎን ሠራዊታችንን ለማሰለፍ ዝግጅት እያደረገ በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳዩ በሽምግልና አንዲቋጭ እንደ ገለልተኛ አካል የመኖችን ለመቅረብ ሙከራ አድርጓል። አስቂኝ በሆነው የመለስ አካሄድ የተደመሙት የመኖች በይፋ እንዳስታወቁት ‘መለስ ገለልተኛ’ ነው ብለው እንደማይቀበሉ እና ይልቁንም እሱና ኢሳይያስ አፈወርቂ ያንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ መሆናቸውን እንደሚያውቁ በትዝብት መልክ አሳፍረው ይመልሱታል።)
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ጦር ከኤርትራ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ ለመዋጋት የሚያስችለውን ዝግጅት እያፋጠነ ነበር። አንድ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቅ የጦር መኮንን አንዳረጋገጠው "ውጊያ እንድንገባ ትዕዛዝ ተሰጠን - በአለባበሳችም ሆነ በማናቸውም ወታደራዊ ትጥቅ ረገድ የኤርትራ ወታደር መስለን እንድንታይ ጥብቅ መመሪያ ተሰጠን - ብንማረክ ወይ አስክሬናችን የመኖች እጅ ቢወድቅ በሚል የኤርትራ ወታደራዊ መታወቂያ ተቀበልን። በመጨረሻም ሌሊቱን ስንገሰግስ አድረን በወሎ ባቲ በማድረግ ኤርትራ ቁጥጥር ስር ወዳለው የአፋር ግዛት ገባን። ተሻግረንም አሰብ ወደብ በመድረስ ወደ አውደ ውጊያው ተቀላቀልን። ይህ ሁሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝብ አንዳችም መረጃ አልደረሰውም - የሞቱ ወታደሮቻችን እሬሳ ሳይነሳ ቤተሰቦቻቸውም ምንም አይነት መርዶ ሳይነገራቸው ተዳፍኖ ተድበስብሶ አለፈ።"
በአራተኛ ክፍለ ጦር ስብሰባ ላይ ሃየሎም የሰነዘረው ብርቱ ተቃውሞ ወሬ ግን ሾልኮ ለሠራዊቱ ደርሷል። መለስ ዜናዊ ከኤርትራ ጋር በፈጠረው ልዩ ግንኙነት የተነሳ በስልጣኑ ላይ አደጋ እያንዣበበ ቢሆንም ለዚህ አደጋ ዋንኛ ተጠሪ ተደርጎ የተቆጠረው ሃየሎም አርአያ ያንን ተቃውሞ ባሰማ ሁለተኛ ወር ላይ በመዝናኛ ሥፍራ "በሰካራም ጥይት’ ተደብድቦ እንዲገደል ተደረገ። ከግድያው ጀርባ የቆሙት ሁለቱ ‘ያንድ ሳንቲም ገፅታዎች’ - መለስ እና ኢሳይያስ ያቀዱትን ከግብ አደረሱ።
በቅርቡ ከኤርትራ መንግስት ከድቶ የወጣ ውስጥ አዋቂ በዝርዝር እንደገለፀው የግድያው መሪ ተዋናይ እንደሚከተለው ቀርበዋል፦ ኡመር ገብረወይኒ (ኢትዮጵያ ውስጥ በንግድ እንቅስቃሴ በመሳተፍ እስከ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ድረስ አዲስ አበባ ይኖር የነበረ ፤ የኤርትራ ደህንነት ተቋም አባል የሆነ እና የኡመር ገብረወይኒ ልጅ (ሃየሎም ከመገደሉ ሁለት ሳምንታት በፊት አዲስ አበባ የተላከ እና ግድያውን ለማቀላጠፍ መሪ ሚና የተጫወተ) ፤ በሻለቃ ፀሐዬ ወልደስላሴ እጅ የተገደለው የወያኔ ደህንነት ሹም ክንፈ ገብረመድህን ፤ አሁን የኢትዮጵያ ደህንነት ሹም የሆነው ጌታቸው አሰፋ ፤ የጌታቸው አሰፋ ሚስት ወንድም የሆነ ወጣት (በሹፌርነት ከኤርትራ ለመጣው ‘አንግዳ’ ለኡመር ገብረወይኒ ልጅ አገልግሎት እንዲሰጥ የተመደበ - ግን ምን እየተካሄደ መሆኑን በዝርዝር የማያውቅ) ፤ አሰፋ ጉሬዛ (ነባር የህወሃት የደህንነት አባል እና ከሃየሎም ግድያ በኋላ ገዳዩን እንዲመረምር የተመደበ ፤ ልዑል የሁዋላ (የህወሃት ነባር አባል እና የደህነነት ሠራተኛ - ናይሮቢ ኬንያ ተመድቦ ‘መወገድ’ የሚገባቸውን ሰዎች ግድያ አቀነባባሪ - እና በመጨረሻም ሃየሎምን ለመግደል የሽጉጥ ምላጭ እንዲስብ ግዳጅ የተሰጠው ጀሚል ያሲን።
እነኝህ ግለሰቦች በሃየሎም አርአያ ግድያ ሴራ ውስጥ ምን ሚና እንደተጫወቱ እና አሁን የት እንደደረሱ በሚቀጥለው ዘገባ እናቀርባለን።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment